ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ኤች አይ ቪ ኤድስ እና ስነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት
የዓለም ኤደስ ቀን ምክንያት በማድረግ ለተማሪዎች እና ዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ የተላለፈ መልዕክት
በመጀመሪያ ዉድ ተማሪዎቻችን እንኳን ለ2011 ዓ.ም በሰላም አረሳችሁ እንዲሁም ወደ መቀሌ
ዩኒቨርሲቲ በደህና መጣችሁ!
ህዳር
22 (December 1) የዓለም ኤድስ ቀን እየተባለ በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በ2011
ዓ.ም ወይም 2018 በአሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘’Know Your Status!’’ በሚል መሪ ቃል ለ 30ኛ ጊዜ ሲከበር በኣገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ‘’ለኤች አይ ቪ ይበልጥ ተጋላጭ ነን፤ እንመርመር ራሳችንን እንወቅ !’’ በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡
የበአሉ መሪ ቃል እንደሚያመለክተዉ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በፈቃደኝነት የኤች አይ ቪ ደም ምርመራ በማድረግ እያዳንዱ ሰዉ ያለበትን
ሁኔታ ማወቅ አለበት ማለት ነዉ፡፡
በዩኒቨርሲቲያችን
ደረጃ የዘንድሮዉን የዓለም ኤድስ ቀን በየግቢዎቻችን በአስተባባሪዎቻችንና በአቻ ለአቻ ተማሪዎች ክለብ በኩል የተለያዩ የህትመት
ዉጤቶችን በመጠቀም አስተማሪ መልዕክቶችን እያስተላለፍን በአሉን እያከበረን እንገኛለን፡፡
በአሁኑ
ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ በኤ ች አይ ቪ እና ስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች መከላከል እና መቆጣጠር ስራዎች የመዘናጋት አዘማሚያ ይታያል፡፡
ነገር ግን ይህ ማለት ኤች አይ ቪ የለም ወይም ጠፍቷል ማለት እንዳልሆነ
ለተማሪዎቻችና የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ አንዳንድ በአገር አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የቫይረሱ
ስርጭት እንደገና እያገረሸ እና አዳዲስ በቫይረሱ የተጠቁ ወገኞች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ በቫይረሱ እየተጠቁ ካሉት
የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሆኑ ጥናቶቹ ያሳያሉ፡፡
መንግስቴ ረብሶ (ዶ/ር)
እያንዳንዳችን
ደማችን በመመርመር ያለንበትን ሁኔታ እስካላወቅን ድረስ ከቫይረሱ ነጻ ነን ማለት ስለማንችል ተማሪዎቻችን በፈቃደኝነት የኤች አይ
ቪ ኤድስ ደም ምርመራ በማድርግ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንዳለባቸዉ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ በዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚማሩ
ወጣቶች ለኤች አይ ቪ እና ስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎች መሆናቸዉ ይታወቃል፡፡ ወጣቶችን ለኤ ች አይ
ቪ እና ስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ከሚያጋልጧቸዉ ምክንያቶች በዋናነት ያለቅድመ ዝግጅት ወሲብ እንዲፈጽሙ የሚያደርግ የአቻ ግፊት
፣ ጥንቃቄ ወደ ጎደለዉ ወሲብ የሚመሩ አጋላጭ ሁኔታዎች (ለምሳሌ፡- ጫት፣ አልኮል፣ ሃሺሽ፣ ወሲብ ተኮር ፊልሞችና
ድረ - ገጾችን ማየት)፣ ለአንድ ወንድ/ ሴት ጓደኛ ታማኝ አለመሆን፣
በርካታ የወሲብ አጋሮች መኖር፣ ግብረስጋ ግንኙነት በሚፈጽሙበት ጊዜ ኮንዶም አለመጠቀም፣ ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ወሲብ መፈጸም ወዘተ
ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡
ስለሆነም ተማሪዎቻችን ወደ ዩኒቨርሲቲ
ሲመጡ ዋና ዓላማቸዉ ትምህርት እና ትምህርት ብቻ መሆን አለበት፡፡ እንዲሁም ጤነኛ እና ዉጤታማ አገር ተረካቢ አምራች ሃይል ሆነዉ
እንዲወጡ ከላይ የጠቀስኳቸዉን ለኤች አይ ቪ እና ስነ ተዋልዶ ጤና
ችግሮች አጋላጭ ሁኔታዎችና
ባሪያት ራሳቸዉን በመጠበቅ ወይም በመቆጠብ ከቫይረሱ ነጻ ሆነዉ ትምህርታቸዉን
በስኬት ማጠናቀቅ ይችላሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲዉ ዉስጥ የኤች አይ ቪ ኤድሰ እና ስነተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመከላከል ተማሪዎቻችን መታቀብ፣
መታመን፣ ኮንዶምን በአግባቡና በቋሚነት መጠቀም፣ ከአደጋ ተጋላጭነት ወደራቁ ጓደኞች ማዘንበል፣ ለፍቅር አጋር የወሲብ ታሪክን በፍጹም
ታማኝነትን መናገር፣ በማይመች አደገኛ ሁኔታ ዉስጥ ሲሆኑ አላስፈላጊ ግፊትን መቋቋም፣ ለወደፊት ህይወት ማቀድና ግልጥ የሆነ የህወት
ግብ ማስቀመጥ፣ የኤች አይ ቪ ምክርና ምርመራ ማድረግ፣ ጫት፣ አልኮል፣ ሃሺሽ እና አደገኛ
ዕጾችን አለመጠቀም፣ ወሲብ ተኮር ፊልሞችና ድረ - ገጾችን አለማየት እና አገልግሎቶችን መፈለግ እንዳለባቸዉ ላሳስባቸዉ እወዳለሁ፡፡
አሁንም ትኩረት ለኤች አይ ቪ መከላከል!
መንግስቴ ረብሶ (ዶ/ር)
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ኤች አይ ቪ ኤድስ እና ስነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች
ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ
ከልብ እናስባለን!